+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ነባር እግረኛ መንገዶችን የማዘመን እና የጥገና ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ምቹና ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶችን በመዘርጋት ለአገልግሎት ለማብቃት የሚያስችሉ ስራዎችን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች በተለያዩ የከተማዋ ማዕዘናት መገንባታቸው የእግረኞችን እንቅስቃሴ ምቹ ከማድረጉም ባሻገር የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ እግረኛ መንገዶች ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት ለከተማዋ ተጨማሪ ውብ ገፅታን እያላበሰ ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ከ159 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ በጀት በተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ በሚገኙት የእግረኛ መንገዶች ሥራ ላይ 28 ማህበራት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቁ እና በመገንባት ላይ ያሉ የእግረኛ መንገዶች በአጠቃላይ 9.6 ኪ.ሜ ርዝመት እና በአማካይ 3.5 ሜትር የጐን ስፋት አላቸው፡፡ የእግረኛ መንገድ የመልሶ ግንባታና ጥገና ስራ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥ ከሜክስኮ – ትንባሆ ሞሎፖል፣ ከአፍሪካ ህብረት – ኦርቢስ፣ ከቀይ መስቀል – ኢትዮ ቴሌኮም ዋና መስሪያቤት፣ ከፖስታ ቤት – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር – ጨፌ ሜዳ፣ ከውሃ ልማት – አትላስ – ሩዋንዳ፣ ከጉርድ ሾላ – 49 ማዞሪያ፣ ከጐሮ – አይ.ሲ.ቲ ፖርክ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡በግንባታ ላይ ያሉ እና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የእግረኛ መንገዶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለታለመላቸው አላማ ብቻ እንዲውሉና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በአካባቢው የሚገኙ የእግረኛ መንገዶችን እንዲንከባከብ ባለስልጣን መ/ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም በማንኛውም እግረኛ መንገድ ላይ የግል ስራ መስራት፣ ተሽከራከሪ ማቆም፣ የንግድ ስራ ማከናወን፣ ማጠር፣ የግንባታና ተረፈ ምርት ቁሳቁስ ማከማቸትና መጠቀም፣ ደረቅ ቆሻሻ ማከማቸትና መጣል፣ የማስታወቂያ ቦርዶች መትከል፣ መቆፈርና ሌሎችም ህገወጥ ተግባራት መፈፀም የተከለከሉ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገበት ይህን ችግር በሚፈጥሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከደንብ ማስከበርና ከፖሊስ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን ህጋዊ እርማጃ የሚወሰድ መሆኑን እያስታወቀ ህብረተሰቡ ይህን ህገወጥ ድርጊት በመከላከልና በመቀነስ በኩል ድርሻውን እንዲወጣ ባለስልጣን መ/ቤቱ ያስታውቃል፡፡

5 Responses to “ነባር እግረኛ መንገዶችን የማዘመን እና የጥገና ስራ እየተከናወነ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *