የአውጉስታ – ወይራ የመንገድ ፕሮጀክትን በተሻለ የግንባታ ፍጥነት ለማከናወን እየተሰራ ይገኛል
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም፡- ከአውግስታ- ወይራ መጋጠሚያ ድረስ እየተገነባ የሚገኘውን የመንገድ ፕሮጀክት በተሻለ የግንባታ ፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ 1.4 ኪ.ሜ ውስጥ 900 ሜትር የሚሆነውን በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ ተጠሪ መሀንዲስ ሚካኤል ስዩም ገልፀዋል፡፡ኢንጂነር ሚካኤል አክለውም የመንገድ ፕሮጀክቱ የግንባታ ጥራቱን ጠብቆ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን በመንገድ ፕሮጀክቱ የወሰን ክልል ውስጥ ያልተነሱ 11 የግልና የቀበሌ ቤቶችን ለማስነሳት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘፈነወርቅ ተካ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ ከተጀመረ 2 ዓመት የሞላው ቢሆንም አሁን ላይ ከወሰን ማስከበር ነፃ በሆኑ ቦታዎች ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታ፣ የገረጋንቲ አፈር ሙሌት፣ የድጋፍ ግንብ፣ የድልድይ እና የከልቨርት ቦክስ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡ይህን የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ቲ.ኤን.ቲ ኮንስትራክሽን ከ308 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባው የሚገኝ ሲሆን ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ የተባለ አማካሪ ደርጅት ደግሞ የማማከር እና የቁጥጥር ስራውን እየተከታተለ ይገኛል፡፡የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከጦር ኃይሎች ወደ ቶታል ከሚወስደው የቀለበት መንገድ በመገንጠል በአውግስታ ወደ ወይራ፣ ቤተል አደባባይ፤ እንዲሁም ከአውግስታ በወይራ መጋጠሚያ ወደ ዘነበ ወርቅና አየር ጤና አደባባይ ለመሄድ አማራጭ መንገድ በመሆን ያገለግላል፡፡