ዓድዋ የብልፅግና ጉዟችን ስንቅ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ቃል በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል። በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ድሉ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የጀግንነት ታላቅ ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዓድዋ ጀግኖች ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በሉዓላዊነትና በብሔራዊ ክብር ላይ በመመካከራቸው ኢትዮጵያን የማትደፈር አገር አድርገው አፅንተውልናል ብለዋል። “ዛሬም እኛ የዚህ ዘመን ትውልድ ልዩነቶቻችንን በውይይት እየፈታን ለብሔራዊ ጥቅም ዘብ ልንቆም ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የአሁኑ ዘመን አርበኝነት በልማት ሥራዎች መለካት እንዳለበት የጠቀሱት ከንቲባዋ፤
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ የስንዴ አብዮትና የምግብ ዋስትና ግዙፍ ፕሮጀክቶች የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ድሎች ብለዋቸዋል ።
ከንቲባ አዳነች በተጨማሪም በኢፍትሐዊነት የተዘጋውን የባሕር በር በማስከፈትና የተጀመሩ የከተማ ትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን በማሳካት የኢትዮጵያን አይቀሬ ብልፅግና ለማረጋገጥ መላው ሕዝብ በቁርጠኝነት እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።


Previous Post
Next Post
Users Today : 53
Users Last 7 days : 323
Users Last 30 days : 1178