የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ ስጋት ታሳቢ ያደረገ የካናል ግንባታ ስራ እያከናወነ ነው
ባለስልጣኑ በአያት ቁጥር ሁለት የጋራ መኖሪያ መንደር ውስጥ 600 ሜትር ርዝመት እና ከ3.5 እስከ 4.5 ሜትር ከፍታ ያለው የውሃ መተላለፊያ መስመር ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ግንባታው ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የጋራ መኖሪያ መንደሮቹ ሲገነቡ የተቆፈረና ሳይነሳ ለረጅም ጊዜ የተከማቸ ምልስ አፈር እየተንሸራተተ ለነዋሪዎች ስጋትን በመፍጠሩ ነው፡፡ በተጨማሪም በክረምት ወራት ከተራራው ቁልቁል የሚወርደውና ከአካባቢው ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጣው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ የጎርፍ አደጋ እንዳያስከትልም ጭምር ነው፡፡ ባለስልጣኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የካናል ግንባታ ስራ በሶስት ተመራቂ የስራ ተቋራጭ አማካኝነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ለግንባታው ስራው ከ32.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተይዞለታል፡፡ ግንባታው አሁን ላይ ከ48 በመቶ በላይ የተከወነ ሲሆን ቀሪ የግንባታ ስራዎችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግት ለማብቃት እየተሰራ ነው፡፡