ዛሬ ማለዳ ከኡራኤል ብራስ፣ ቦሌ መድኃኔዓለም ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን ገምግመናል።
ይህ ኮሪደር በከተማችን በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትን ለማስፋት የተጀመረ ዘጠነኛው ኮሪደር ሲሆን፣ አጠቃላይ 11.5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን እና በውስጡ በርካታ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎችን የያዘ ነው። የግንባታው ሂደትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ከኮሪደሩ በተጨማሪም ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ታሪካዊውን የፒኮክ ወይም በጥንታዊ መጠሪያ ስሙ ማዕከላዊ ፓርክን ከወንዝ ዳርቻ ጋር አያይዘን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያለማነው ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ሌላኛው የስበት ማዕከል፣ ድንቅና ውብ ስፍራ ሆኖ እየተገነባ ነው።
በተለይም የCOP 32 ጉባኤ በሚከናወንበት በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመዉ የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህ አጋጣሚ የCOP 32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ፣ ይህ ጉባኤ በመዲናችን መዘጋጀቱ ከአገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ አገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ የሚፈጥር ስለሆነ ከመቼውም የበለጠ ትኩረት ይሻል።
በመሆኑም መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጦ እንድንጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እንድናደርግ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Previous Post
Next Post
Users Today : 30
Users Last 7 days : 261
Users Last 30 days : 1169