+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የመንገድ ሀብት ላይ ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሱ በሚገኙ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

የደቡብ አዲስ አበባ የመንገድ ኔትዎርክ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት የአስተዳደርና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ አብይ ኪዳኑ፤ ከለቡ-ቫርኔሮ በሚወስደው መንገድ የንግድና የመኖሪያ ህንፃዎች ያለፍቃድ የአስፋልት መንገድ ላይ የኮንክሪት ግንብ በመገንባት ለመኪና መግቢያ መውጫነት በመጠቀም የእግረኛ መንገዶች ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዝናብ ውሃ ወደ ድሬኔጅ መስመር በቀጥታ እንዳይገባ ስለሚሆን የአስፋልት መንገድ በጎርፍ እንዲጥለቀለቅ በማድረግ መንገዱ ሊሰጠው ከሚገባው አገልግሎት ጊዜ በፊት እንዲበላሽ ምክንያት እንደሚሆን አቶ አብይ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦች ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ባለመቻላቸው፤ የደቡብ አዲስ አበባ የመንገድ ኔትዎርክ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በግብረ-ኃይል እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ የመንገድ ሀብትን ከጉዳት ለመከላከል ለህብረተሱ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት እየሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ አብይ፤ ለመንገዶች ብልሽት ምክንያት የሆኑ ህገወጥ ተግባራትን መከላከል ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

Comments are closed.