ከ3.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ ሀብት ላይ ደረሰ
አዲስ አበባ የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም፡- በተሽከርካሪ ግጭት ምክንያት በከተማዋ መንገዶች ላይ ከ3.9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ደርሷል፡፡በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በቀለበት መንገድ ላይ 26 ግጭቶች የደረሱ ሲሆን ከቀለበት መንገድ ውጭ ባሉ መንገዶች ላይ ደግሞ 126 የግጭት አደጋዎች ደርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት በደረሱ 152 የግጭት አደጋዎች ሳቢያ በመንገድ ሀብቶች ላይ ግምቱ 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ጋር 23.1 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው ክትትል ዘንድሮ ለደረሰው የንብረት ውድመት 3.5 ሚሊዮን ብር ካሳ አስከፍሏል፡፡ ይህም የህዝብ ንብረት በሆኑ የመንገድ አካላት ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የሚያመለክት ነው፡፡ በግጭት ጉዳት እየደረሰባቸው ከሚገኙት የመንገድ ሀብቶች መካከል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ በተተከሉ የመንገድ መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ቦርዶች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ይጠቀሳሉ፡፡ በከተማዋ ጤናማ ትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ባላቸው በመንገድ አካላት ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለው ጉዳት ለከፋ የትራፊክ አደጋ መንስኤ ስለሚሆን አሽከርካሪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲያሽከረክሩ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ያሳስባል፡፡