የባለስልጣኑ ሠራተኞች የኮቪድ 19 ክትባት እየወሰዱ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ሠራተኞች ለ2ኛ ዙር የኮቪድ 19 ክትባት እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡የባለስልጣኑ መካከለኛ ክሊኒክ ኃላፊ አቶ አለማየሁ አበበ እንደገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሠራተኞች የስራ ባህሪያቸውን በመረዳት በስራ ቦታቸው እንዲከተቡ ልዩ ፈቃድ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡አቶ አለማየሁ አክለውም ከዚህ በፊት ከ600 በላይ የሚሆኑ የባለስልጣኑ ሠራተኞች የተለያዩ የክትባት ዓይነቶችን መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተከተቡ ሰዎች ክትባቱን ደግመው መከተባቸው በሽታ የመከላከል አቅማቸውን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ አሁን ላይ ከዚህ በፊት የተከተቡም ሆነ ያልተከተቡ ሠራተኞች ክትባቱን በመውሰድ ራሳቸውን ከኮሮና ወረርሽ እንዲጠብቁ አቶ አለማየሁ አሳስበዋል፡፡ክትባቱን ሲወስዱ ያነጋገርናቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል በበኩላቸው ክትባቱ በመስሪያ ቤታችን መሰጠቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ሁሉም ሰው ክትባቱን ወስዶ ራሱን ከአስከፊ ህመምና የሞት አደጋ መከላከል ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡