+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከ20 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመንገድ ዲዛይን ማኑዋልና ስፔስፊኬሽን ሊሻሻል ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከ20 ዓመታት በላይ ሲገለገልባቸው የቆየውን የዲዛይን ማንዋል ፣ ጋይድ ላይን እና የስታንዳርድ ስፔስፊኬሽን ለማሻሻል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ባለስልጣኑ በትላንትናው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል የዲዛይን ማኑዋል ጥናት መጀመሩን ለማብሰርና ተጨማሪ አዳዲስ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን ለመሰብሰብ በከተማዋ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት፣ ከተለያዩ አማካሪ ድርጅቶች እና ከተመረጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በማብሰሪያ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የተቋሙ የዲዛይን ማኑዋል ረጅም ዓመታት ከማገልገሉም ባሻገር ብዙ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን አውስተው ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዘርፉ ላይ ያሉ አዳዲስ እውቀቶችን እና እድገቶችን ለማካተት ሲባል በአዲስ መልክ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አዲሱ የዲዛይን ማኑዋል የዩቲሊቲ፣ የመንገድ ደህንነት፣ የላንድ ስኬፕ፣ የትራንስፖርት ፕላኒንግ፣ የመንገድ ሀብት አስተዳደርን፣የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥናቶችን በማካተት ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ የሚጠናቀቅ ሰነድ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ይህ የዲዛይን ማኑዋል በዓለም ባንክ ድጋፍ ዳር አል- ሀንዳሳህ በተባለ ዓለም ዓቀፍ ከፍተኛ ልምድ ባለው አማካሪ ድርጅት እተዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን በ 2 ዓመት ጊዜ ውስጥም ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አያይዘውም የዲዛይን ማኑዋሉ ዝግጅት ተጠናቆ ተግባር ላይ ሲውል የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ መሠረተ ልማት አቅርቦት ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር ከተማዋ ከሌሎች አቻ ዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የሚወዳደር የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንዲኖሯት ከማስቻሉም በላይ አሁን ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ የትራፊክ መጨናነቅ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ነባሩ የዲዛይን ማኑዋል ብዙ የአሰራር ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ጠቁመው ለቀጣይ ጊዜ አዲሱ የዲዛይን ማኑዋል ዝግጅት መጀመሩ ከተማዋ ሁሉን ዓቀፍ የሆነ አጠቃላይ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንዲኖራት ያስችላታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.