የመንገድ ዳር መብራቶች ለከተማችን በምሽት ድምቀትንና ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቾትን የሚለግሱ የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው
ታህሳስ 19 ቀን 2015ዓ.ም፡- የጎዳና ላይ መብራቶች፤ በከተማዋ ያለውን የምሽት የትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆን ያስችላሉ፡፡
እግረኞች በምሽት በሠላም ወጥተው እንዲገቡ፣ ከአደጋ የፀዳ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና የዜጎች ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና የሚያበረክቱ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ በከፍተኛ ወጪ በተሰሩ የመንገድ ዳር መብራቶች ላይ የተለያዩ ህገወጥ ተግባራት ይፈፀማሉ፡፡ ከነዚህ ተግባራት መካከል የትራንስፎርመር፣የኬብል፣የብሬከር፣የፊዊዝ ስርቆት፣በመሰረተ ልማት ተቋማት በሚፈፀም የመንገድ ቁፋሮ እንዲሁም አንዳንድ ግለሰቦች የስርቆት ወንጀል ለመፈፀም እንዲያመቻቸው የመንገድ ዳር መብራት የማበላሸት ተግባር ይፈፅማሉ፡፡
በተጨማሪም በተሽከርካሪ ግጭት ሳቢያ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የመንገድ መብራት አገልግሎት መቆራረጥ እያጋጠመ ይገኛል፡፡
በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚፈፀም ስርቆት እና በተሸከርካሪ ግጭት ምክኒያት የመንገድ ዳር መብራቶች ብልሽት ከሚያጋጥማቸው አካባቢዎች መካከል ከሀይሌ ጋርመንት – ቱሉዲምቱ – ጎሮ፣ ከአያት አደባባይ – ቦሌ አራብሳ፣ ከአያት አደባባይ – ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ – ጎሮ፣ ከጎጃም በር – ሸጎሌ – ዊንጌት እና ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ የመንገድ ዳር መብራቶችን ከጉዳትም ሆነ ከስርቆት መጠበቅ የራሱን ህይወት ከአደጋ መጠበቅ መሆኑን በመረዳት በአግባቡ እንዲገለገልባቸው እንዲሁም የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርስን ጉዳት ወይም ስርቆት ሲመለከት በነፃ የስልክ መስመር 8267 በመደወል ወይም በአካባቢው ወደ ሚገኙ የመንገድ ሃብት አስተዳዳር ጽ/ቤቶች በአካል በመቅረብ ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር ባለስልጣኑ ጥሪ ያቀርባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity