ከአጉስታ – ወይራ ሰፈር አቋራጭ የመንገድ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም፡-በተለምዶ አጉስታ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እስከ ወይራ መጋጠሚያ ድረስ አቋራጭ የመንገድ ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ 1.5 ኪ.ሜ ውስጥ 600 ሜትር የሚሆነው የሰብ ቤዝ ፣ የድልድይ እና የከርቭ ስቶን ስራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪው የመንገዱ ክፍል ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታና የካፒንግ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥም አስፋልት ለማልበስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምም 50.1 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡
ይህን የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ቲኤን ቲ ኮንስትራክሽን /TNT construction / ከ308.3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባው የሚገኝ ሲሆን ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ የተባለ አማካሪ ደርጅት ደግሞ የማማከር እና የቁጥጥሩን ስራ እየተከታተለው ነው፡፡
የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከጦር ሀይሎች ወደ ቶታል በሚወስደው የውጪ ቀለበት መንገዱን በመያዝ በአውግስታ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወይራና ቤተል አደባባይ ለመሄድ አቋራጭ መንገድ በመሆን ያገለግላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity