“አካታች የፈጠራ ስራ እና ሽግግራዊ መፍትሄ” በሚል መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞች ቀን ተከበረ
አዲስ አበባ፣ህዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራር እና ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ለ30ኛ ጊዜ “አካታች የፈጠራ ስራ እና ሽግግራዊ መፍትሄ” በሚል መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞችን ቀን በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ እያሱ ሰሎሞን በከተማዋ 100 ኪ.ሜትር ርቀት የሚሸፍን ነባር የእግረኛ መንገዶችን መልሶ በመገንባት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባለስልጣኑ የአካል ጉዳተኞችን ተጨባጭ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ምቹና የተሻለ የመንገድ መሰረተ ልማት ለመገንባት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ እያሱ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የአዲስ ህይወት አይነ ስውራን ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሪት አፄባዩሽ አበበ በበኩላቸው የመሰረተ ልማቶች እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሲገነቡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆናቸውን ባለድረሻ አካላት የሆኑ ሁሉ ትኩረት ሰጥተው ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወ/ት ፀደንያ አበበ በጎጂ ልማድ፣ በተዛባ አመለካከት እንዲሁም በህግ ክፍተት ምክንያት አካል ጉዳተኞች ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እና የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞችም ባለስልጣኑ በመዲነዋ የሚገነቡ መንገዶች ከዲዛይን ዝግጅት ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን አካታች ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
