የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞች የፀረሙስና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ የበኩላቸውን ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋገጡ
19ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
አዲስ አበባ፣ ህዳር 23 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ሙስናን መታገል በተግባር” በሚል መሪ ሀሳብ በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎሞን እንደገለፁት ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ሀገራችን የገጠማትን ፈታኝ ውጣ ውረዶች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሙስና እና ብልሹ አሰራር ላይ የተሰማሩ አካላት የዘረጉት ያልተገባ የጥቅም ትስስር በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ላይ እንቅፋት ከመደቀን ባለፈ በዜጎች የኑሮ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ የሚገኘው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው፣ አሁን ላይ መንግሥት የጀመረው የተጠናከረ የፀረሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን በተሰለፍንበት የሥራ መሰክ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ የፀረሙስና ትግል አጋርነታችንን በተግባር ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል።
ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት የመነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለስልጣን መስሪያቤቱ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ደመቀች መንገሻ በበኩላቸው ሙስና ከፍተኛ እውቀት፣ ስልጣንና ገንዘብ ባላቸው ሰዎች ጭምር የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ቢያደርገውም፣ ዋነኛ ምንጩ የስነ ምግባር ጉድለት በመሆኑ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡ በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞችም መንግሥት የጀመረውን የተጠናከረ የፀረሙስና ትግል በመደገፍ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን በመከላከል ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ ሀሳብ ያቀረቡት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት የፀረሙስና ትግሉ ምንም ያህል ፈታኝና ውስብስብ ቢሆንም በሀገር እድገትና በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት የከፋ በመሆኑ በተግባር በሚገለፁ እንቅስቃሴዎች የፀረሙስና ትግሉን በመደገፍ፣ ብልሹ አሰራሮችን በመታገልና የሞራል ልዕልናን በመገንባት ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የፀዳች ሀገር ለአዲሱ ትውልድ ለማስረከብ የባለስልጣን መስሪያቤቱ መላ ሠራተኞችየበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
