+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከአፍሪካ ህንፃ- ጀሞ መስታወት ፋብሪካ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 68.2 በመቶ ላይ ደርሷል

አዲስ አበባ ፣ህዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በተለምዶ አፍሪካ ህንፃ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጀምሮ እስከ ጀሞ መስታወት ፋብሪካ የሚደርሰው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 68.2 በመቶ አፈፃፀም ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 1.6 ኪ.ሜ ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ ስራው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል እየተከናወነ ይገኛል፡፡

አሁን ላይ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች መካከል የቤዝ ኮርስ፣ የከርቭ ስቶን፣የሰብ ቤዝ፣የካፒንግ፣ የአፈር ቆረጣ፣ የቦክስ ከልቨርት፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታና የድልድይ ግንባታ ስራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ባለስልጣኑ ይህን የመንገድ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ከመንገድ ፕሮጀክቱ የወሰን ክልል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያልተነሱ የመብራት ፖሎች፣ የውሀ መስመሮች እና የቤት አጥሮች በመኖራቸው የግንባታ ስራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡

ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው የመንገድ ፕሮጀክቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲወጡ ባለስልጣኑ መልክቱን ያስተላልፋል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከአየር ጤና አደባባይ ወደ ጀሞ ሶስት መሄድ ለሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ሚካኤል አደባባይ ሳይደርሱ የቀለበት መንገዱን የዳር መስመር በመያዝና ወደ ቀኝ በመታጠፍ በቀጥታ በጀሞ መስታወት ፋብሪካ በኩል ወደ ጀሞ ሶስት አደባባይ ለመውጣት ያስችላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.