የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29 ቀን 2015ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከ100 በላይ ለሚሆኑ የባለስልጣኑ ሴት ሰራተኞች የጡት ካንስር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወይዘሪት ፀደኒያ አበበ እንደገለፁት በጥቅምት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውለውን የጡት ካንሰር ቀን ምክንያት በማድረግ በጡት ካንስር ምንነት፣ ምልክትና የሚያስከትለው ጉዳት ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለባለስልጣኑ ሴት ሰራተኞች ተሰጥቷል፡፡
ወይዘሪት ፀደኒያ አያይዘውም የጡት ካንሰር በወቅቱ ከተደረሰበት በህክምና መከላለከል የሚቻል መሆኑን ጠቁመው፣ነገር ግን በሽታው ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ከተዛመተ የመዳን እድሉ ዝቅተኛ በመሆኑ የጡት ካንሰር ምልክት የታየባቸው ሴት ሰራተኞች ወደ ባለስልጣኑ ክሊኒክ በመሄድ የህክምና ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው ስለጡት ካንሰር ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ እንደረዳቸው ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የጡት ካንሰር በኢትዮጵያ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሰ መምጣቱን ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ ቀናትም በባለስልጣን መስሪያቤቱ ሎቶች በተመሳሳይ ስልጠናው እንደሚሰጥ ከሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የጡት ካንሰር ሴቶችን ከሚያጠቁ በጣም የተለመዱ የካንሰር አይነቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ በመላው ዓለም በየዓመቱ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች ለጡት ካንሰር ይጋለጣሉ፡፡ በኢትዮጵያም በካንሰር ከሚጠቁ ታማሚዎች መካከል 34 በመቶ የሚሆኑት ለጡት ካንሰር ተጋላጭ እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity