የአያት – ጣፎ ማስፋፍያ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከአያት ወደ ጣፎ የሚወስደውን አስፋልት መንገድ የማስፋፍያ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት አደረገ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ የነባር መንገዶች ማሻሻያ እና አዳዲስ መንገዶች ግንባታ ሥራ በማከናወን ለትራፊክ ክፍት እያደረገ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ 3.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 6 ሜትር የጎን ስፋት ያለውን የአያት-ጣፎ ማስፋፍያ ፕሮጀክት ግንባታ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት አድርጓል፡፡
ነባሩ የአያት – ጣፎ መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ እያስተናገደ በመሆኑ ሳቢያ ከፍተኛ መጨናነቅ ይታይበት የነበረ ሲሆን፣ በመንገዱ ሁለቱም አቅጣጫ በኩል አንድ ረድፍ ተጨማሪ መኪኖችን ማስተላለፍ የሚያስችል የአስፋልት መንገድ ማስፋፊያ ግንባታ በማከናወን ቀደም ሲል በአካባቢው ይታይ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ መቀነስ ተችሏል፡፡
በመዲናዋ ከሚገኙ የመውጪያ እና መግቢያ መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የአያት- ጣፎ መንገድ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በአያት እና በካራ መስመር የሚስተዋለውን የትራፊክ መጭናነቅ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደ የካ አባዶ እና ጣፎ አካባቢ ለሚሄዱ ተሸከርካሪዎች የተሳለጠ የትራፊክ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/addisababaroads/
