ዝክረ ጥቅምት 24 በባለስልጣን መስሪያቤቱ ታስቦዋለ
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም፡- “ጥቅምት 24 መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት የሚዘክር ሁለተኛ ዓመት የመታሰቢያ መርሀ ግብር የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የባለስልጣን መስሪያቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት በዛሬውዕለትታስቧል፡፡
የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት “ጥቅምት 24 መቼም አንረሳውም” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች የምንዘክረው ይህ ዕለት፤ ምንጊዜም ለመከላከያ ሠራዊታችን ያለንን የማይናወጥ ክብርና አጋርነት የምንገልፅበት ሁነት ከመሆኑም ባሻገር፣ የሀገር መከታና ጋሻ በሆነው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈፀመው አሳፋሪ ተግባር መቼም ቢሆን በሀገራችን ውስጥ እንዲከሰት ፈፅሞ የማንፈቅድ መሆኑን በጋራ ድምፃችንን የምናሰማበት መልካም አጋጣሚ በመሆኑም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም፤ መከላከያ ሠራዊታችን ጥቅምት 24 በከፈለው መስዋዕትነት እና ዛሬም ድረስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ለህዝቦቿ ክብር በየአውደ ግንባሩ ግንባሩን ሳያጥፍ እያካሄደ ባለው ወታደራዊ ኦፕሬሽን ጠላቶቻችን እንደተመኙልን ሳይሆን፣ ዛሬም እንደትናንቱ በነፃነትና በአብሮነት በጋራ እንድንቆም አስችሎናልና እጅግ ከፍ ባለ ክብር ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችንን ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ሁሉም የልማት ውጥኖቻችን ከዳር ደርሰው የምንጓጓለት ሀገራዊ ብልፅግና እውን የሚሆነው፣ ሀገራችን ሠላሟ ሲጠበቅ መሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አያይዘውም አሁን የታዩ የሠላም ተስፋዎች ይበልጥ አብበውና ፍሬ አፍርተው፣ የህዝባችን መከራና ሰቆቃ ያከትም ዘንድ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ለማበርከት ዝግጁ እንድንሆን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሥነ-ስርዓቱ ተሣታፊዎች በበኩላቸው፤ ለጦርነቱ እልባት ለመስጠት በደቡብ አፍሪካ በተካሄው ድርድር የተደረሰበት ስምምነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ መልካም ሁኔታ እንዲፈጠር በየጦር ግንባሩ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው የጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን አበርክትዎ የላቀ በመሆኑ ያላቸውን ከፍ ያለ አክብሮት ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/addisababaroads/
