የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን 5ኛው የህብረት ስምምነት ሰነድ ፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንና በተቋሙ የሠራተኛ ማህበር መካከል በተደረገ ድርድር የተዘጋጀው አምስተኛው የህብረት ስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ተፈርሟል።
የህብረት ስምምነቱን በአሠሪው ወገን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንዲሁም በሠራተኛው በኩል የተቋሙ መሰረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል በቀለ ፈርመዋል።
የህብረት ስምምነቱ የሠራተኛውን እና የአሠሪውን መብትና ግዴታዎች በማስጠበቅ በኩል ከሚኖረው ዓይነተኛ ሚና ባሻገር የኢንዱስትሪ ሠላም በማስፈን ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል።
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በአዋጅ ከተቋቋመ ወዲህ አሁን ለ5ኛ ጊዜ ተሻሻሎ የፀደቀው የህብረት ስምምነት አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ባስተላለፉት መልዕክት በህብረት ስምምነቱ ዝግጅት ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የኮሚቴ አባላት ምስጋና አቅርበው፣ መላው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች እጅና ጓንት በመሆን በላቀ የሥራ ተነሳሽነት መንፈስ የከተማችን ነዋሪ በመንገድ መሠረተ-ልማት ዘርፍ የሚጠብቀውን እመርታዊ ለውጥ ለማሳካት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።
የተቋሙ መሰረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል በቀለ በበኩላቸው ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የህብረት ስምምነቱ ተሻሽሎ እንዲዘጋጅና እንዲፀድቅ በማድረግ በኩል ለነበረው ሚና በሠራተኛው ስም ምስጋና አቅርበው፣ ለኢንዱስትሪው ሠላም መስፈንና ለተቋሙ ተልዕኮ ስኬት የሠራተኛ ማህበሩ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity