+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በኮንትራት አስተዳደር ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰጥ የቆየው ዓለም አቀፍ የፊዲክ ስልጠና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የሥራ መሪዎችና ባሙያዎች የተካፈሉበት እና ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ፊዲክ /FIDIC/ በተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ለለፉት አስር ቀናት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ሲያካሄድ የቆየው የኮንትራት አስተዳደር ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

በሥልጠናው መዝጊያ ሥነስርዓት ላይ ተገኝተውመልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ የስልጠና ዕድሉን ያገኙ የምህንድስና ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪውን በእውቀትና በክህሎት ለመምራት የሚያስችላቸው ከፍተኛ ልምድ ያገኙበት ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማህበር በስልጠናው ላይ የተሳተፉት ዶክተር ኢንጂነር ውብሸት ዠቃለ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው ፊዲክ FIDIC/ በኮንትራት አስተዳደር ዙሪያ የስራ ላይ ስልጠና መሰጠት መቻሉ በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ዘርፍ እንደ ሀገር ያሉብንን ችግሮች ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ስልጠና መሆኑን አውስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የምህንድስና ዘርፍ ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኢንጂነር ወንድወሰን ማሞ በበኩላቸው ስልጠናው በኮንትራት አስተዳደርና በምህንድስና ግዥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታት የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ዓለም የደረሰበትን የእውቀት ደረጃ ማየት የቻልንበትና ከፍተኛ ልምድ የቀሰምነበት ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ስልጠና ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተጨማሪ ከኮንስትራክሽን የሙያ ማህበራት፣ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ በአጠቃላይ 110 የሚሆኑ የምህንድስና እና ሌሎች ባለሙያዎች ተሳትፈዋል

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.