በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት በደረሰባቸው መንገዶች ላይ የሚካሄደው የጥገና ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2015ዓ.ም፡- የአዲስ አባባ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙና ለብልሽት የተጋለጡ መንገዶችን በመለየት የጥገና ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡
ባለስልጣን መስርያ ቤቱ ከአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ሥራው ጎን ለጎን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተጋለጡ መንገዶችን በመለየት የተበላሸውን የአስፋልት ክፍል ቆርጦ በማንሳትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በመጠገን በከተማዋ ምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር የጀመረውን የጥገና ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
አሁን ላይ የአስፋልት ጥገና እየተከናወነ ከሚገኙባቸው አካባቢዎች መካከል ከላፍቶ 58 – ሳሪስ ዳማ ሆቴል እንዲሁም ጎሮ-ጃክሮስ አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ባለስልጣን መስርያቤቱ የጀመረውን የመንገድ ጥገና ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል በሌሎች የከተማዋ ማዕዘናት ጉዳት የደረሰባቸውን መንገዶች በመጠገን ምቹ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር በትኩረት ይሰራል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity