+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በዓለም አቀፍ የምህንድስና ውል ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ ነዉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም፡- ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ፊዲክ(FIDIC) የዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች የውል ሰነዶች አዘገጃጀትና አተገባበር ላይ ያተኮረ ለ10 ቀናት የሚቆይ ሰልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

ስልጠናው ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን እና ከሌሎች አቻ ተቋማት የተውጣጡ 110 ሰልጣኞችን ያከተተ ሲሆን ከመስከረም 30 ቀን ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በመሰጠት ላይ ነው፡፡

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት ሥልጠናው አንድ ዓለም አቀፍ የምህንድስና ግዥ በሚዘጋጅበት ወቅት ሊሟሉ የሚገባቸውን ዋና ዋና መስፈርቶች እና በውል ሰነዶች አዘገጃጀት ላይ ሰልጣኞች የበለጠ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ እና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት ይህን የሥልጠና እድል ማግኘቱ የፕሮጀክቶችን ውለታ በከፍተኛ ጥንቃቄ ለማስተዳደር የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ ወደ ግንባታ የሚገቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የምህንድስና ግዢዎችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በውል ማስተዳደር ሂደት የሚያጋጥሙ የውል ለውጥና ማሻሻያ፣ የክፍያ ማስተካከያና አፈፃፀም፣ እንዲሁም በተዋዋዮች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሚፈቱባቸው ሁኔታዎች እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉን የባለሙያዎች አቅም በማጎልበት ፕሮጀክቶች በተመደበላቸው በጀት፣ በውል በተቀመጠላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ ልክ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በበጀት ዓመቱ የዝግጅት ምዕራፍ በተለያዩ የሥልጠና መስኮች የተቋሙን አመራርና ሠራተኞች የመፈፀም አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡ https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.