በመንገድ ዳር የውሀ መፋሰሻ መስመሮች ላይ በሚደርስ ጉዳት ሳቢያ የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ነው
ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የውሀ መፋሰሻ መስመሮችን በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት የጎርፍ አደጋ እየተከሰተ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት ወራት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመቀነስ እና የመንገድ ሀብቱን ደህንነት ለማረጋገጥ በበጋው ወራት መጠነ ሰፊ የድሬኔጅ መስመሮች ፅዳትና ጥገና ሥራዎች ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም የፍሳሽ መስመሮችን በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት የጎርፍ አደጋዎች መከሰት ጀምረዋል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ዘነበወርቅ አዲሱ መናኸሪያ አካባቢ ግንቦት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የጣለው ዝናብ የጎርፍ አደጋ አስከትሎ በዘጠኝ አባወራ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
ለጐርፍ አደጋው መንስኤ የሆነው በአካባቢው የሚገኝ የውኃ መፋሰሻ መስመር በቆሻሻ በመደፈኑ እና አለአግባብ ከመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ጋር እንዲገናኝ በመደረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የውሃ መፋሰሻ መስመሩ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ የጎርፍ ውሃው ከመተላለፊያ መስመሩ ገንፍሎ በመውጣት ወደ አካባቢው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት በመግባት ጉዳት አድርሷል፡፡
በወቅቱ የጎርፍ አደጋ መረጃው የደረሰው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ጥገና ባለሙያዎችን በፍጥነት ወደ ሥፍራው በመላክ በቆሻሻ የተደፈነው የውሃ መፋሰሻ መስመር እንዲከፈት በማድረግ ጎርፉ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በመጪዎቹ የክረምት ወራት ሊከሰቱ የሚችሉ የጐርፍ አደጋ ስጋቶችን ከወዲሁ ለማስቀረት የውሃ መፋሰሻ መስመሮችን ደህንነት መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ መላው ከተማችን ነዋሪዎች ደረቅ ቆሻሻ እና የተለያዩ ጠጣር ነገሮችን ወደ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ባለመጣል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያሳስባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads