ከወሎ ሰፈር-ኡራኤል መዳረሻ አካባቢ የመንገድ መጋጠሚያ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከወሎ ሰፈር ወደ ኡራኤል በሚወስደው አዲሱ መንገድ መዳረሻ አካባቢ የመንገድ መጋጠሚያ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል::
ግንባታው አጠቃላይ 140 ሜትር የሚሆን ርዝመት ያለው ሲሆን የትራፊክ መብራት ተከላውን ጨምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል ከአትላስ ወደ ወሎ ሰፈር ለመሄድ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች የግድ ኡራኤል አደባባይን እንዲሁም ከወሎ ሰፈር ወደ ኡራኤል የሚሄዱ ደግሞ አትላስ ድልድይ አካባቢ ባለው መታጠፊያ ለመዞር ይገደዱ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር በአካባቢው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ሲፈጥር መቆየቱ ይታወቃል፡፡
አሁን ላይ ይህ የመጋጠሚያ ግንባታ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሲጠናቀቅ የትራፊክ መብራት ተተክሎለት ከወሎ ሰፈር ወደ ኡራኤል እና ከአትላስ ወደ ወሎ ሰፈር በስተግራ ለሚታጠፉ አሽከርካሪዎች የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲፈጠርላቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡