+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

መጪውን የክረምት ወራት ታሳቢ ያደረገ የድሬኔጅ መስመር ግንባታና ጥገና ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ግንቦት 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መጪውን የክረምት ወራት ታሳቢ ያደረጉ የመንገድ ዳር የዝናብ ውሀ መፋሰሻ /ድሬኔጅ/ መስመሮች የግንባታ እና ጥገና ስራዎችን በስፋት እያከናወነ ነው፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተጋለጡ የመንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮችን በመለየት በበጋው ወራት እንደጉዳት መጠናቸው የግንባታና የጥገና ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በተለይም መጪውን የክረምት ወቅት ታሳቢ በማድረግ ለጐርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት እንደየ ችግሮቹ ደረጃ የማስተካከያ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በተጨማሪም በአጠቃቀም ችግር ምክንት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የድሬኔጅ መስመሮችን በመፈተሽ የውሃ መውረጃ መስመሮችን የፅዳት፣ የመጠገን እና የመልሶ የመገንባት ስራዎችን በመከናወን ላይ ነው፡፡

የጥገና ስራ እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል መስከረም ት/ቤት፣ ቤተ መንግስት አካባቢ፣ ልደታ ፀበል አካባቢ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አካባቢ፣ ፈረንሳይ 41 እየሱስ፣ አያት ዞን 6፣ አያት ጣፎ፣ ራዲካል ት/ቤት አካባቢ፣ መገናኛ እና አማኑኤል አካባቢ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በቀጣይም በክረምት ወራት ለጐርፍ ስጋት ናቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የድሬኔጅ ፅዳት፣ ጥገናና ግንባታ ስራዎች አጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ሁሉም ሕብረተሰብ በአካባቢው የሚገኙ የመንገድ ዳር የዝናብ መፋሰሻ መስመሮች በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም የበኩልን አውንታዊ ድርሻ እንዲወጣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity

Comments are closed.