+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የቂርቆስ ማርገጃ – ቡልጋርያ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የአስፋልት ማልበስ ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ሃይል እየተከናወነ የሚገኘው የቂርቆስ ማርገጃ – ቡልጋርያ ፕሮጀክት የአስፋልት ማልበስ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በራስ ሃይል እየገነባው ያለው ይህ የቂርቆስ ማርገጃ – ቡልጋርያ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት የግንባታ ስራው መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ርዝመት 1.2 ኪሎ ሜትር ሲሆን 20 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡

ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ከአጠቃላይ የመንገዱ ርዝመት 700 ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የመጀመርያ ደረጃ አስፋልት ማልበስ ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን 300 ሜትር የፓይፕ ቀበራ እና ተያዥ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ በፕሮጀክቱ መጨረሻ አከባቢ ወደ ቂርቆስ ቤተ ክርስትያን የሚወስደው መስመር ላይ በ200 ሜትር የመንገድ ክልል ውስጥ የሚገኙ የቴሌ እና የመብራት ኮንኩሪት ምሰሶዎች እንዲሁም ቤቶች ባለመነሳታቸው ምክንያት ቀሪ የመንገድ ግንባታ ሥራውን ለማከናወን እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

ስለሆነም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ግዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በፕሮጀክቱ የመንገድ የወሰን ውስጥ የሚገኙ መሰረተ-ልማቶችን በማዘዋወር እና ቤቶችን በማስነሳት በኩል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት በፍጥነት እንዲወጡ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ይህ መንገድ ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሲሆን ከቄራ ወደ ለገሃር እና ቂርቆስ ቤተክርስትያን አካባቢ መሄድ ለሚፈልጉ አሽከርካሪዎች በአቋራጭነት በማገልገል በአካባቢው ላይ ያለውን የትራፊክ ጫና የሚያቃልል ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ :-

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/አባባጭትይ

ዩ-ቲዩብ : https://m.youtube.com/channel/UCylJ2yBcsMuIWIz6nSIjfpQ

Comments are closed.