+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በተለምዶ ጀርመን አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ ድልድይ የጥገና እና የጽዳት ስራ እያከናወነ ነው፡፡

ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በድልድዮች እና በወንዞች ዳርቻ አካባቢ በሚደፋ የግንባታ ተረፈ ምርት፣ አፈርና ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት ለጐርፍ መጥለቅልቅ ስጋት የሆኑ ድልድዮችን በመለየት የጥገና እና የማስተካከያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡የጥገና እና የማስተካከያ ስራዎች እየተከናወነ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መሀከል አንዱ በተለምዶ ጀርመን አደባባይ አካባቢ የሚገኘው ድልድይ ነው፡፡ በዚህ ድልድይ አካባቢ ለረጅም ጊዜያት ይደፋ በነበረ አፈር፣ ቆሻሻ እንዲሁም የወንዙን ዳርቻ ተከትሎ በሚከናወኑ የችግኝ ማፍላትና የጓሮ አትክልት ሥራዎች ምክንያት የወንዙ ተፈጥሮአዊ የመፍሰሻ መንገድ በመጥበቡ ባለፈው ዓመት ክረምት ወራት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሰዎች ህይወት ማለፉና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመጪው የክረምት ወራት ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ በድልድዩ ስር ለረጅም ጊዜ የተከማቸውን ቆሻሻ እና ደለል በማንሳት ወንዙ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ተብቆ የሚጓዝበትን ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ ችግሩን ይበልጥ እያባባሱ ከሚገኙ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል በወንዙ ዳርቻ እና በድልድዩ አካባቢ በተደጋጋሚ እየተደፋ የሚገኘው አፈር፣ ልዩ ልዩ የግንባታ ተረፈ ምርቶች እንዲሁም በአካባቢው በሚከናወነው የችግኝ ማፍላት እና የጓሮ አትክልት ልማት ምክንያት የወንዙ ተፈጥሯዊ ፍሰት በመስተጓጎሉ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡በቀጣይም በወንዞች መዳረሻ እና በድልድዮች አካባቢ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ተግባራት ምክንያት የሚደርሱ የመንገድ መሰረተ-ልማት ጉዳቶች እና በንብረትና በሰው ህይወት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢው ነዋሪዎች የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ ባለስልጣኑ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

Comments are closed.