የሕብረተሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳልጡ ድልድዮች ግንባታና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚገኙና ለጉዳት የተጋለጡ ድልድዮችን በመልሶ ግንባታና ጥገና ደረጃ እየሥራ ይገኛል።ባለስልጣኑ በዕቅድ ከያዛቸው ዘርፈ ብዙ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታና ጥገና ስራዎች መካከል በከተማዋ የተለያዩ ማዕዘናት የሚገኙ ድልድዮችን የአገልግሎት ደረጃ ለማሻሻል አዲስ ግንባታና በመልሶ ግንባታ ደረጃ የሚያከናውነው ጥገና ስራ አንዱ ነው፡፡ አዲስ እየተገነቡ ከሚገኙ ድልድዮች መካከል ሲ.ኤም.ሲ በርታ የመኖሪያ መንደር አካባቢ የሚገኙ 2 ድልድዮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በአካባቢው በሶስት ቦታዎች ላይ ከሚገነቡት ድልድዮች መካከል የአንዱን ድልድይ የግንባታ ስራ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ቀሪ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን የሁለተኛው ድልድይ የቁፋሮ ስራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡ከዚህም በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠትና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው እና ለከባድ ብልሽት የተዳረጉ ድልድዮችን በመለየት በመልሶ ግንባታ ደረጃ የጥገና ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡እንደ አዲስ ፈርሰው በመገንባት ላይ ከሚገኙት ድልድዮች መካከል በተለምዶ ኮካ ድልድይ እና ካራቆሬ አካባቢ አቤል ድልድይ ተብለው የሚጠሩት ድልድዮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አዲስ የተገነቡትም ሆነ ጥገና እየተደረገላቸው የሚገኙ ድልድዮች ረዥም ጊዜ አገልግሎት መስጠት ይችሉ ዘንድ ሕብረተሰቡ በድልድዮች ላይ የሚፈፀሙ ከህገ-ወጥ ተግባራትን በመከላከልና በመጠበቅ ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡