የሙያ ደህንነትና የመሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም፡- በግንባታ ወቅት ሊከሰት የሚችልን አደጋ ለመከለከል የሚያስችል የሙያ ደህንነትና የመሳሪያዎች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡ የስልጠናው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባለስልጣኑ የስራ አካባቢ ደህንነት ክትትል ቡድን መሪ አቶ ዘውዴ ማሞ እንደገለፁት በተለያዩ ስራ ቦታ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠናው መሰጠቱ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ባሻገር ሰራተኞች ለራሳቸውና ለሌሎች ሰራተኞች የስራ ላይ ደህንነት በበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያሉ ሰራተኞች ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ቦታ እንዲኖራቸውና ራሳቸውን ከማንኛውም አደጋ ለመጠበቅ የሚረዳ ስልጠና እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ስልጠናው በግንባታ ስራ ላይ መደረግ የሚገባቸውን የደህንነት ጥንቃቄዎች፣ የአደጋ መንስኤዎችና የመከላከያ ዘዴዎችን በተመለከተ ከፅንሰ ሀሳብ ባሻገር የተለያዩ ተቋማትን ተሞክሮ እና በሥራ አካባቢ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የሚያግዝ ነው።