የኮዬ ፈቼ ኮንዶሚኒየም ፕሮጀክት 18 የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም፡- በኮዬ ፈቼ የጋራ መኖሪያ መንደሮች ፕሮጀክት 18 ሎት 2 የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል፡፡ይህን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አይ.ኤፍ. ኤች ኢንጂነሪንግ የተባለው ሥራ ተቋራጭ ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባው የሚገኝ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ትራንስ ናሽናል ኢንጂነሪንግ እያከናወነ ይገኛል፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ 8.4 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ10 እስከ 30 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት አለው፡፡ አሁን ላይ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ ርዝመት ውስጥ 6.3 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የአስፋልት ንጣፍ ስራ በመገባደድ ላይ ሲሆን፣ ቀሪው 1.9 ኪሎ ሜትር ሚሆነው የመንገድ ክፍል ደግሞ በኮብል ንጣፍ ሙሉ በሙሉ ተሸፍኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የፊዚካል አፈፃፀምም 65 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ይሁን እንጂ 200 ሜትር ገደማ በሚሆነው የመንገድ ፕሮጀክቱ ክፍል ላይ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች፣ ዛፎች እና የቤት አጥር እስካሁን ድረስ ባለመነሳታቸው ምንም ዓይነት የግንባታ ስራ ማከናወን አልተቻለም፡፡በመሆኑም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ የወሰን ማስከበር ችግሩን በመፍታት የመንገድ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡