በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አተገባበር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ውይይት ተደረገ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 4 ቀን 2014 ፣- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በመንገድ ግንባታ ሂደት እያጋጠሙት የሚገኙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያግዝ ውይይት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር አካሂዷል፡፡ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልእልት ግደይ እንደገለፁት በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙት የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈፃፀም የተሻለ መሆኑ በመስክ ጉብኝት የታየ ቢሆንም በአንፃሩም አንዳንድ የመንገድ ፕሮጄክቶች እያጋጠማቸው የሚገኘው የወሰን ማስከበር ችግር በፍጥነት ባለመፈታቱ ለግንባታ ሥራዎች መዘግየት ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታም ቋሚ ኮሚቴው የሚያካሂደውን ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል ፡፡የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ድረስ ለመንገድ ግንባታ ዘርፍ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸቸውን አቅርበው፣ በቀጣይም ከበጀትና ከወሰን ማስከበር ጋር እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮች እንዲፈቱ በማድረገ በኩል የተለመደው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የሚያጋጥሙት የወሰን እና ተያያዥ ችግሮች በወቅቱ እንዲፈቱ በቀጣይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያካሂደውን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡