+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለስልጣኑ በቀጣይ ሶስት ወራት ተጨማሪ የመንገድ ኘሮጀክቶችን አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4 ቀን 2014 ዓ.ም፡- ይህ የተገለፀው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ9 ወራት የስራ አፈፃፀሙን በገመገመበት ወቅት ነው፡፡ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩን የመሩት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በከተማዋ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀው ከነዚህ ውስጥም እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ መንገዶችን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ኢንጂነር ሞገስ አክለውም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ባለስልጣኑ ሊያከናውን ካቀዳቸው ስራዎች በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከተማዋ ያስተናገደቻቸው ልዩ ልዩ ሀገራዊ ሁነቶች በተሳካ መልኩ እንዲከናወኑ በመንገድ ጥገና እና አንስላሪ ሥራዎች ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉ ለባለስልጣኑ ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ባለስልጣን መስሪያቤቱ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 581.8 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና የጥገና ስራዎች ለማከናወን አቅዶ 597.24 ኪሎ ሜትር በማከናወን ከእቅዱ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል፡፡ባለፉት ዘጠኝ ወራት በእቅድ አፈፃፀም ሂደት እንደ ችግር ከታዩ ጉዳዮች መካከል የበጀት እና የግብዓት እጥረት እንዲሁም ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ ችግሮቹ እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

Comments are closed.