ከአውቶቢስ ተራ- መሳለሚያ- 18 ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ የወሰን ማስከበር ችግር ፈተና ሆኗል
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ ከአውቶቢስ ተራ-መሳለሚያ እስከ ኮልፌ ቀለበት መንገድ ድረስ እየተገነባ ለሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የወሰን ማስከበር ስራዎች በወቅቱ አለመጠናቀቃቸው በግንባታ ሂደቱ ላይ ከፍተኛ ፈተና ሆኗል፡፡ግንባታው ከተጀመረ ሁለት ዓመት ገደማ ያስቆጠረው ይህ የመንገድ ፕሮጀክት አሁን ላይ ካለው አጠቃላይ 3.35 ኪ.ሜ ርዝመት ውስጥ 700 ሜትር የሚሆነው ብቻ በመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ተከናውኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለምዶ ሻንቅላ ወንዝ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ 52 ሜትር ርዝመት ያለው ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታም እየተከናወነ ይገኛል፡፡አሁን ላይ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምም 12.47 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ቀሪው የመንገድ ክፍል ግን የወሰን ማስከበር ስራው ባለመጠናቀቁ የግንባታ ስራ ለማከናወን አዳጋች ሆኗል፡፡በዚህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ በአጠቃላይ 198 ቤቶች፤ 249 የሚሆኑ የመብራት እና የቴሌ ፖሎች ከመንገድ ፕሮጀክቱ የወሰን ክልል ውስጥ ባለመነሳታቸው ምክንያት በግንባታ ስራው ላይ መሰናክል እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን ቻይና ሬል ወይ ሰቨንዝ ግሩፕ የተባለ ዓለም አቀፍ የስራ ተቋራጭ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባው ሲሆን ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ደግሞ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን እየተከታተለው ይገኛል፡፡ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ ችግር ለማቃለል እና የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የወሰን ማስከበር ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ርብርብ እንዲያደርጉ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡: