+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለስልጣኑ በ9 ወራት ውስጥ 74 በመቶ የወሰን ማስከበር ስራዎችን አከናወነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በተያዘው በጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ 3157 ልዩ ልዩ የወሰን ማስከበር ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ 2 ሺ 338 በማከናወን የዕቅዱን 74 በመቶ አከናውኗል፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በግንባታ ላይ ከሚገኙ የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የወሰን ክልል ውስጥ 565 ቤቶች፣ አንድ ሺ 407 የመብራት ፖሎች እና 366 የቴሌ ምሰስዎችን ለማስነሳት ችሏል፡፡ይሁን እንጂ አሁን ላይ በተለያዩ የግንባታ ሳይቶች ላይ በርካታ የወሰን ማስከበር ስራዎች ባለመነሳታቸው በመንገድ ፕሮጀክቹ ግንባታ ላይ ከፍተኛ መጓተት እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡በአሁኑ ወቅት በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት የግንባታ ስራቸው እየተጓተተ ከሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከአውግስተ ወይራ፣ ኤምፔሪያል ማሰላጫ፣ ከቦሌ ኤርፖርት ገርጂ፣ ቦሌ ሚካኤል የላይና የታች ድልድይ፣ ከቃሊቲ ቶታል አቃቂ ድልድይ ቱሉ ድምቱ፣ ከፋፋ ምግብ ፋብሪካ ዳማ ሆቴል ብሐሬ ፅጌ ሰኔ 9 ት/ቤት፣ ከናይጀሪያ ኤምባሲ ቀጨኔ፣ ከአውቶቢስ ተራ መሳለሚያ፣ ከቡልጋሪያ ማዞሪያ ቂርቆስ ማርገጃ እና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ባለስልጣኑ እነዚህን የወሰን ማስከበር ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የከተማ፣ የክ/ከተማ እና የመሰረተ ልማት ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

Comments are closed.