የሲ ኤም ሲ – ሰሚት መደኃኒዓለም መንገድ ግንባታ የወሰን ማከበር ችግር ተፅእኖ ፈጥሮበታል
መጋቢት 23/2014 ዓ.ም – አዲስ አበባ፡- ከሲ.ኤም.ሲ ተነስቶ – ሰሚት መደኃኒዓለም የሚዘልቀው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ስራው በወቅቱ ባለመጠናቀቁ በግንባታ ስራው ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል፡፡የግንባታ ስራው በህዳር ወር 2013 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ባጋጠመው የወሰን ማከበር ችግር ምክንያት ስራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በወቅቱ ማከናወን አልተቻለም፡፡ መንገዱ በአጠቃላይ 3.2 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር የጎን ስፋት ኖሮት እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ 1.2 ኪሎ ሜትር በሚሆነው የግንባታ ክፍል ላይ ብቻ የቱቦ ቀበራና የሰብ ቤዝ ዝግጅት ስራዎችን ለማከናወን ተችሏል፡፡በአሁኑ ወቅት በቀሪው የግንባታ ክፍል ላይ የወሰን ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ከ120 በላይ የግለሰብ ቤቶች፣ የመብራት ሀይል ምሰሶዎች፣ የቴሌ መስመር እንዲሁም የውሃና ፍሳሽ መስመር በግንባታ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ጥሪውን ያቀርባል፡፡የሲ ኤም ሲ – ሰሚት መደኃኒዓለም መንገድ ግንባታ ስራ በራማ ኮንስትራክሽን አማኝነት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ፎርትረስት አማካሪ ድርጅት ደግሞ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ የግንባታ ስራ ሲጠናቀቅ ወደ የተባበሩት፣ ሰሚት፣ ፊጋ እና አካባቢው መሄድ ለሚፈልጉ አሽከርካሪዎች በአቋራጭነት በማገልገል በአካባቢው ላይ ያለውን የትራፊክ ጫና የሚያቃልል ይሆናል፡፡