የሰሚት 40/60 ኮንዶሚንየም የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በተሻለ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ፡- የሰሚት 40/60 ኮንዶሚኒየም የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በተሻለ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በግንቦት ወር መጨረሻ 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን 1 ኪ.ሜትር ርዝመትና ከ8-15 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡ አሁን ላይ 260 ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የድሬነጅ መስመር ዝርጋታ እና የአፈር ሙሌት ስራው ተጠናቆ የሰብ ቤዝ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ዓጠቃላይ አፈፃፀሙም 28 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡ይሁን እንጂ በመንገዱ ወሰን ላይ ያሉ የወሰን ማስከበር ችግሮች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ባለመነሳታቸው ግንባታው በታሰበው ፍጥነት እንዳይከናወን ተፅኖ አሳድረዋል፡፡በመንገድ ፕሮጀክቱ ውስጥ ከሚገኙ ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራዎች መካከል የመብራት ፖል እና የግለሰቦች አጥር ይገኙበታል፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራዎችን ለማስነሳት በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆኑ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡