ኢትዮጵያ COP32ን ለማስተናገድ መመረጧ ለሀገራችን ሰፊ የኢኮኖሚ እድል ይፈጥራል
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ይህንን ታሪካዊ እድል የእንግዶችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በመፍጠር በሚገባ ለመጠቀም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸዉ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የአየርንብረት ለውጥ ማሕቀፍ ኮንቬንሽን አባል ሀገራት COP32ን ለማዘጋጀት መመረጧ የዲፕሎማሲያዊ ድል ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ትልቅ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የሚፈጥር ነው።
በተባበሩት መንግሥታት የአየርንብረት ለውጥ ማሕቀፍ ኮንቬንሽን መሠረት የኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሀገር መሆኗ በሁሉም መስክ የሚፈጥዉ መልካም እድል ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
COP32ን ማስተናገድ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን ያመጣል፡፡ ከ50 እስከ 70 ሺህ ተሳታፊዎች የሚሳተፉበት ኮንፍረንስ ሲሆን የሀገር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአየር ንብረት ባለሙያዎች፣ የሚዲያ ቡድኖች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የግል ኩባንያዎች ይሳተፉበታል፡፡
ይህን ያህል ተሳታፊ ለሳምንት በሚዘልቀዉ ቆይታዉ በሀገራችን ኢኮኖሚ ዉስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ የሆቴሎች፣ የምግብ ቤቶች፣ የመጓጓዣ እና የመዝናኛ ስፍራ አገልግሎቶች ፍላጎት በእጅጉ የሚጨምር ሲሆን በዘርፉ የሚኖረዉ መነቃቃትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዉ ቀላል አይደለም፡፡
ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች እና በተለያዩ መስኮች ለተሰማሩ ባለሙያዎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ በሮችን ይከፍታል፡፡ ለመስተንግዶ፣ ቱሪዝም፣ ሎጂስቲክስ እና አይሲቲ ባሉ ዘርፎች እድገት የላቀ አስተዋጽኢ ያበረክታል፡፡ መላዉ ኢትዮጵያዊያን በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ይህንን ታሪካዊ እድል የእንግዶችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በመፍጠር በሚገባ ለመጠቀም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸዉ፡፡
መንግስት ጉባኤዉ የተሳካ እንዲሆን ብሄራዊ ኮሚቴ በማዋቀር በልዩ ሁኔታ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን የኮፕ 32 ተወካይ ፕሬዝደንት አድርጎ መድቧል፡፡ ዶክተር ጌዲዮን ከሀገር ውስጥ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት አካላት እና አለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የኮፕ 32 ዝግጅትን የሚመሩ ይሆናል።


Previous Post
Next Post
Users Today : 30
Users Last 7 days : 261
Users Last 30 days : 1169