+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ወደ ኮልፌ የግብርና ምርት መሸጫ የገበያ ማዕከል የሚወስደው መንገድ በግንባታ ላይ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ከቤቴል እሳት አደጋ ወደ ኮልፌ የግብርና ምርት መሸጫ የገበያ ማዕከል የሚወስደውን የኮብል መንገድ በአስፋልት ደረጃ እየገነባ ይገኛል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ቀደምሲል 520 ሜትር ርዝመት የሚሸፍነውን የመንገዱን ክፍል አጠናቆ ለአገልግሎት ያበቃ ሲሆን አሁን ላይ 677 ሜትር ርዝመት እና የእግረኛ መንገድ ጨምሮ 20 ሜትር የጎን ስፋት የሚሸፍነውን ቀሪውን የመንገድ ክፍል በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል፡፡

ግንባታው በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ራስ ኃይል ምዕራብ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት በቀንና በምሽት ክፍለ ጊዜ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፤ አሁን ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የገረጋንቲ ሙሌት፣ የትቦ ቀበራ ፣ የከርቭስቶን፣ የሰቤዝ እና ተያያዥ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከአንፎ ወደ ቤቴል እሳት አደጋ እና ተቃራኒ አቅጣጫ ለሚጓዙ አሸከርካሪዎች አማራጭ መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም ባሻገር፣ ለኮልፌ ቀራኒዮ የግብርና ምርቶች መሸጫ የገበያ ማዕከል የትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ይሆናል፡፡

Comments are closed.