በ2ኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከ60 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጠረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ከ60 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል አለ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) እንዳሉት፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ከ60 ሺህ ለሚልቁ እንዲሁም በመጀመሪያው ዙር ከ52 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡
አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ ቦታዎችን የቱሪስት መዳረሻ እና መዝናኛ በማድረግ ገቢ እንዲያመነጩ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሲጠናቀቁ ደግሞ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠሩ ጠቁመዋል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ፤ የካሳንቺስ- እስጢፋኖስ-መስቀል ዐደባባይ- ሜክሲኮ- ቸርችል-አራት ኪሎ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ሥራ፣ የጫካ ፕሮጀክት (ሳውዝ ጌት)- መገናኛ- ሃያ ሁለት- መስቀል ዐደባባይ ኮሪደር፣ ሲኤምሲ- ሰሚት- ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር እና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ሳር ቤት-ካርል ዐደባባይ-ብስራተ ገብርኤል-አቦ ማዞሪያ-ላፍቶ ዐደባባይ-ሃና ፉሪ ኮሪደር፣ አንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ- ጎሮ ኮሪደር፣ አራት ኪሎ- ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል ኮሪደር፣ ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር እና እንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደርን ማካተቱ ይታወቃል፡፡
በአጠቃላይም ከ130 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚሸፍን ነው የተገለጸው፡፡
ምንጭ፦ FBC
