+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች በ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ፤ በመጀመርያው ሩብ ዓመት ከዝግጅት ስራዎች ባሻገር፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን የከተማዋን አስፋልት መንገዶች ለአንድ ወር በዘለቀ የዘመቻ ስራ በመጠገን የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ የተሳለጠ ለማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ኢንጂነር ሙህዲን አያይዘውም በመጀመርያው ሩብ ዓመት የተገኙ ስኬቶችና መልካም ተሞክሮችን በማሳደግ፣ በቀጣይ ወራትም የተቋሙን ውጤታማነት ለማስቀጠል ሁሉም የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በላቀ ተነሳሽነት እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፀጋዬ ቦርሴ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ መንገዶች ጥራታቸው ተጠብቆ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የከተማዋን የመንገድ መሠረተ-ልማት ሽፋን ለማሳደግና ደረጃውን ለማሻሻል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፤ በአገልግሎት ላይ የሚገኘውን የመንገድ ሀብት በአግባቡ መጠቀምና መንከባከብ እንደሚገባ የጠቆሙት የባለሥልጣኑ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አወል ሰይድ፤ በበጀት ዓመቱ ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ ጥገና ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ሩብ ዓመት፤ ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበሩ መንገዶችን በመጠገን በከተማዋ ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ሰፊ ሥራ የተከናወነበት ወቅት መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር መሐመድ አወል፤ የመንገድ ሀብቱን ለብልሽት የሚያጋልጡ ህገወጥ ድርጊቶችን በመቆጣጠር በኩል የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ይበልጥ ተቀናጅተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የተቋም ለውጥ እና ድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል ዶሌቦ በበኩላቸው፡ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይችል ዘንድ፤ በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በመጨረሻም ለአንድ ወር በቆየው ልዩ የመንገድ ጥገና የዘመቻ ስራ እና በሌሎች የመንገድ መሠረተ-ልማት መስኮች የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሥራ መሪዎችና ሰራተኞች የማበረታቻ ሽልማትና የምስጋና የምስክር ወረቅት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

ዩቱዩብ:- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369

ቲክቶክ፡- https://www.tiktok.com/@addisababaroads

ድረ-ገፃችንን ይጎብኙ ፡- https://www.aacra.gov.et

ለማንኛውም ጥቆማ ፡- 8267 ነጻ የስልክ መስመር ይጠቀሙ

Comments are closed.