አረንጓዴ አሻራችን ደምቆ ለውጤት እንዲበቃ – ነቃ!
ልክ እንደ አለፉት ዓመታት ሁሉ፣ ዘንድሮም በሀገር አቀፉ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ፤ ዛሬን የምናጌጥበትና በረከቱ ለነገው ትውልድ የሚተርፍ አረንጓዴ አሻራችንን ማሳረፍ ጀምረናል፡፡
ይህ ሰናይ ተግባር ከራሳችን አልፎ ቀጣዩ ትውልድ በምቹ ከባቢ አየር ውስጥ የሚኖርበትን ዕድል ከማስፋቱም ባሻገር፣ ለዓለም የአየር ንብረት መጠበቅ የማይናቅ ድርሻ እንደሚያበረክት እሙን ነው፡፡ ለዚህም ነው ተግባሩ አኩሪ እና አርዓያነት ያለው ነው የምንለው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ባለፉት ዓመታት በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ በንቃት በመሳተፍ የዚህ አኩሪ የታሪክ አሻራ ተጋሪነታቸውን ለማረጋገጥ ያሳዩት ተነሳሺነትና ትጋት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፡፡
የችግኝ ተከላ ተሳትፏችን ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ የታለመለትን ግብ በላቀ ደረጃ ያሳካ ዘንድ፤ ካለፉት ዓመታት ስኬቶቻችን ተሞክሮ በመውስድ መልካም አፈፃፀማችንን ማሳደግ እና ከጉድለቶቻችን በመማር፤ አረንጓዴ አሻራችን ደምቆ ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
የደን ሃብት ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚሉት፤ ችግኞች የሚተከሉበትን አዲስ አካባቢ ተላምደው በፍጥነት እንዲፀድቁ፣ በችግኝ ተከላ ወቅት ከጉድጋድ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ተከላ ሂደት ድረስ ለችግኞች ተገቢው እንክብካቤና ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የተከልናቸው ችግኞች ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ ሆነው በፍጥነት ማደግ ይችሉ ዘንድ ከለላ ማበጀት ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡
የሰውና የእንስሳት ንክኪ በሚበዛባቸው ስፍራዎች የሚተከሉ ችግኞች እድገታቸው ከመገታቱም ሌላ በቀላሉ ሊጠፉ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑን ደግሞ በአመዛኙ በተለያዩ የመንገድ ዳርቻዎችና አካፋዮች ላይ ተተክለው ሳይፀድቁ የቀሩ ችግኞች ናቸው፡፡
በመሆኑም በተለይ በመንገድ አካፋይና ዳርቻዎች ላይ ችግኝ ተከላ ከማካሄዳችን በፊት፡-
1. የምንተክላቸው የችግኞች ዝርያዎች በመንገድ ሃብታችን ላይ ጉዳት የማያደርሱና የቅርንጫፎቻቸው እድገትም ወደፊት በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ ተፅእኖ እንደማያሳድር ማረጋገጥ፣
2. የችግኝ መትከያ ሥፍራዎች፤ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ በእግረኞች እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ የሚያሳድር አለመሆኑን ጭምር ማረጋገጥ እና፣
3. የተተከሉ ችግኞችን በመከለል ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ በእንክብካቤ እንዲፀድቁ ከየአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በጋራ በመምከር ባለቤት እንዲኖራቸው ማድረግ አረንጓዴ አሻራችን ደምቆ ለውጤት እንዲበቃ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡
በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በወል መክረን፣ መፍትሄ የመስጠት ልምዳችንን ይበልጥ እናጎልብት!
መልካም የችግኝ ተከላ ጊዜ!