የመንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ፅዳት ሥራ በመከናወን ላይ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በአፈር፣ በቆሻሻና መሰል ምክንያቶች የተደፈኑ የድሬኔጅ መስመሮችን በማፅዳትና በመጠገን የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመከላከል እየሠራ ይገኛል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የበጋውን ወራት ጨምሮ መጠን ሰፊ የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና ሥራ እያከናወነ ቢሆንም፤ ዛሬም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በዝናብ ውሃ መውረጃ መስመሮች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚጣለው ደረቅ ቆሻሻ የከተማዋን ፅዳትና ውበት ከማጓደሉም ባሻገር፣ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመንገድ መሠረተ-ልማት ለብልሽት እያጋለጠ ይገኛል፡፡
ለእዚህም ማሳያ ጀሞ መስታዎት ፋብሪካ አካባቢ በክረምት ወቅት መንገዱ በጎርፍ በመጥለቅለቅ የእግረኛ እና የመኪና እንቅስቃሴን ሲያስተጓጉል መቆየቱ የሚጠቀስ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፡ በአካባቢው የሚገኘው ወንዝ ዳርቻ በደለል እየተሸፈነ በመምጣቱ፣ የወንዙ ተፈጥሮአዊ ፍሰት እየተስተጓጎለ የወንዙ ውሃ ወደ የእግረኛ እና የአስፋልት መንገድ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የመንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መውረጃ መስመሮችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች በመታገዝ እያፀዳ ይገኛል።
ለከተማዋ የመንገድ መሰረተ ልማት ብልሽት ምክንያት ከሆኑ ያልተገቡ ተግባራት መካከል፤ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ፣ እንዲሁም በግንባታ ተረፈ ምርት አወጋገድ በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና መላው የከተማዋ ነዋሪ የጋራ መጠቀሚያ ለሆነው መንገድ ሀብት ደህንነት የበኩላቸውን አውንታዊ ሚና እንዲወጡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያሳስባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
ዩቱዩብ:- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369