በወንዞች ዳርቻ የሚፈፀመው ህገ-ወጥ ድርጊት የጎርፍ አደጋ ስጋት ደቅኗል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ፡- በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ከጀርመን አደባባይ ወረድ ብሎ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ በተደጋጋሚ ጊዜያት በሚደፋ አፈር፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት ሳቢያ የወንዙ ተፈጥሯዊ የመፋሰሻ መስመር እየጠበበ በመምጣቱ አሁን ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋቱን አሳሳቢ አድርጎታል።
ከሁለት ዓመት በፊት በአካባቢው በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሰዎች ህይወት ማለፉና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያየ ወቅት የአደጋ ስጋቱን ለመቀነስ በድልድዩ ስር እና በወንዙ ዳርቻ ለረጅም ጊዜ የተከማቸውን እና ከፍተኛ መጠን ያለውን ቆሻሻ እና ደለል አፈር በማንሳት ወንዙ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲጓዝ የሚያስችል የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
ይሁን እንጂ በወንዙ ዳርቻ የሚከናወነው ህገወጥ እንቅስቃሴ ተባብሶ በመቀጠሉ፣ በወንዙ ዳርቻ በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት መፍጠሩን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የክፍለ ከተማው አስተዳደር እና የፀጥታ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የጎርፍ አደጋ ቅድመ-መከላከል ሥራውን በማገዝ በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም በመንገድ ሀብት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ለማስቀረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይም በሌሎች የወንዞች መፋሰሻ መስመሮችና በድልድዮች አካባቢ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ተግባራት የጎርፍ አደጋ ስጋት በመደቀን በሰው ህይወት፣ በንብረትና በመንገድ መሰረተ-ልማት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢው ነዋሪዎች የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ባለስልጣን መስሪያቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
ዩቱዩብ፡- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369