+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለሥልጣኑ ለአቅመ ደካማ ነዋሪ የገነባውን መኖርያ ቤት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በተለምዶ ቶሎሳ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የገነባውን ባለ ሶስት ክፍል መኖሪያ ቤት ከሙሉ የቤት ቁሳቁስ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ በዛሬው ዕለት በይፋ አስረክቧል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከመደበኛ ተልዕኮው በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ቀደም ሲልም በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ የቤቶች እድሳት ማከናወኑን አውስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የባለሥልጣን መስሪያቤቱ ሠራተኞች በቋሚነት ለሚደግፋቸው 50 ህፃናት ድጋፍ እየደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይም መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በባስልጣን መስሪያ ቤቱ ባህል ሆነው እንዲቀጥል እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልፀዋል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጀ ፈይሳ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ከመገንባት በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሣተፍ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የቤት ቁልፍ የተበረከተላቸው ወ/ሮ አልጋነሽ መንግስቴ፤ ቀደም ሲል ይኖሩበት የነበረው ቤት በጣም የተጎዳ፣ በክረምት ወቅት ጎርፍ ይገባበት እንደነበር እና ለመኖርም ምቹ እንዳልነበር ገልፀው፤ አሁን ላይ የዘመናዊ ቤት ባለቤት በመሆናቸው “የጨለመው ህይወቴ አሁን በርቶልኛል” በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በባለሥልጣን መሥሪያቤቱ በጉልበት ሰራተኛነት ለረጅም ዓመታት እያገለገሉ የሚገኙት ወ/ሮ አልጋነሽ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ችግራቸውን ተረድቶ በአዲስ መልክ በተገነባ ቤትና በተሟላ የቤት እቃ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ስላደረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

ዩቱዩብ፡- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369

Comments are closed.