+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ጎሮን ከቦሌ አራብሳ የሚያስተሳስረው የመንገድ ፕሮጀክት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የየረር ነፋሻማና ሰንሰለታማ ተራራዎችን በቅርብ ርቀት የሚያስቃኘው እና የጎሮ አካባቢዎችን – ከቦሌ አራብሳ የጋራ መኖሪያ መንደሮች ጋር በልማት ለማስተሳሰር እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው አዲስ የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የአራብሳ -አይሲቲ ፓርክ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 6 ኪ.ሜ ርዝመትና 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ ስራውን አለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያከናወነው የሚገኝ ሲሆን፣ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ቤዛ አማካሪ ድርጅት እየተከታተለው ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የመንገድ ፕሮጀክቱ ክፍል ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታ፣ የሙሌት እና ተያያዥ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ሲሆን፣ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀሙም 20 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ አሁን በግንባታ ላይ ከሚገኘው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ – ጎሮ የመንገድ ፕሮጀክት ጋር የሚተሳሰር በመሆኑ፤ ከመሐል ከተማ ወደ ጎሮ እና አራብሳ ለመጓዝ ይፈጠር የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡

በተጨማሪም ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፋጠን ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ሌላ የዲዛይን ስራው ላይ የአረንጓዴ ልማትን ያካተተ በመሆኑ ውብና ማራኪ ገፅታን በመፍጠር ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢ ለመገንባት ያግዛል።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

ዩቱዩብ፡- https://www.youtube.com/@addisababacityroadsauthori1369

Comments are closed.