በመዲናዋ እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የመንገድ ደረጃ ከፍ ያደረጉ ናቸው፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ
AMN – የካቲት 16/2016 ዓ.ም
በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ ማዕዘናት እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የመዲናዋን የመንገድ ስታንዳርድ ከፍ ያደረጉ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩን የ2016 ዓ.ም የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለአስተዳደሩ ምክር ቤት አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩን የመንገድ መሠረተ ልማትን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በግማሽ ዓመቱ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ጋር በተያያዘም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ 16.39 ኪ.ሜ የአስፋልት እና የ4.45 ኪ.ሜ የኮብል ስቶን የመንገድ ግንባታ ተከናውኗል።
የ12.71 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ ግንባታና 5.91 ኪ.ሜ የፈጣን አውቶቡስ መንገድም መገንባት መቻሉም ተመልክቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ለአካል ጉዳተኞች በሰጠው ትኩረትም 27.6 ኪ.ሜ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ የእግረኛ መንገድ መገንባት ተችሏልም ብለዋል ከንቲባዋ።
በተለያዩ የከተማዋ ማዕዘናት እየተገነቡ በሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ2 ሺህ 300 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ግዙፍ ተሸጋጋሪ እና የወንዝ መሻገሪያ ድልድዮች እየተገነቡ ነው።
ፕሮጀክቶቹ የትራፊክ አደጋን የሚቀንሱ መሆናቸውን አና 27.6 ኪ.ሜ እርዝመት ያላቸው የእግረኛ እና የሞተር አልባ ትራንስፖርት መንገዶች አሏቸው።
የነዚህ መንገዶች አፈፃፀም ጥሩ በመሆኑም በዚህ ዓመት አብዛኞቹን መንገዶች ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እና እስከ 43 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ያብራሩት ከንቲባዋ፣ የከተማዋን የመንገድ ስታንዳርድ ከፍ ያደረጉ እና የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀንሱ ናቸውም ብለዋል።
በከተማዋ ያሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም በቀሪ ወራት ተገቢ ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው።