+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የመውጫና መግቢያ መንገዶች ግንባታ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም፡- ለአዲስ አበባ የከተማ ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ከሚገኙ የመሠረተ-ልማቶች አንዱ መንገድ ነው፡፡

መንገድ ለአካባቢ ብሎም ለሀገር እድገት መፋጠን ጉልህ ድርሻ ያለው የመሠረተ-ልማት ፍላጎት በመሆኑ፣ ሁልጊዜም የህብረተሰቡ ቀዳሚ ጥያቄ እና የመንግሥትም ቁልፍ የትኩረት አቀጣጫ ሆኖ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፤ የከተማዋን አጠቃላይ እድገትና ድርብርብ የመዲናነት ሚና የሚመጠን፣ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ-ልማት ከመገንባት ጎን ለጎን፣ የከተማዋን ነዋሪዎች የመግቢያና መውጫ የመንገድ ችግር ለማቃለል በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የጠጠር መንገድ ግንባታ ስራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የመውጫና መግቢያ መንገዶች ግንባታ በተለይም አዳዲስ እየለሙ በሚገኙ አካባቢዎች እና የልማት ተነሽዎች በሚኖሩባቸው አዳዲስ የመኖሪያ መንደሮች የሚታየውን የመንገድ ችግር ለማቃለል እና አርሶ አደሩን ከመሃል ከተማ ጋር በቀላሉ ለማገናኘት ታሳቢ ተደርጎ የሚከናወን የመንገድ መሠረተ-ልማት አማራጭ ነው፡፡

ባለሥልጣን መስሪያቤቱ አሁን ላይ በጠጠር ደረጃ የመግቢያና መውጫ መንገድ ግንባታ ስራ እያከናወነባቸው ከሚገኙ ስፍራዎች መካከል፤ ከአራራት ሆቴል ጀርባ 300 ሜትር ገባ ብሎ እየተገነባ የሚገኘው መንገድ ይጠቀሳል፡፡

የጠጠር መንገድ ግንባታ ስራው በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል እየተከናወነ የሚገኘ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 2.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 8 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው፡፡

ስራው ከተጀመረ ከአስራ አምስት ቀናት ያልበለጠ ጊዜን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ የቁፋሮ ስራውን 50 በመቶ ማከናወን ተችሏል፡፡

ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ የግንባታ ወጪ የተመደበለትን ይህን መንገድ በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅም ታቅዷል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ የተለያዩ የአስፋልትና የኮብል መንገዶች ግንባታና ጥገና ስራዎች በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች የጠጠር መንገዶችን በመገንባት የህብረተሰቡን የመውጫና መግቢያ መንገዶች ጥያቄ ለመመለስ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.