ከአያት እስከ ጣፎ የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል
ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ መሠረተ-ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች መካከል የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ አንዱ ነው።
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ አሁን ላይ የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ እያከናወነባቸው ከሚገኝባቸው ሥፍራዎች መካከል ከአያት እስከ ጣፎ ድረስ ያለው የመንገድ ክፍል ይገኝበታል፡፡
በመልሶ ግንባታ ደረጃ እየተሰራ የሚገኘው ይህ የእግረኛ መንገድ በአጠቃላይ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ሲሆን እስከ 4.7 ሜትር የጎን ስፋት አለው።
በ2016 በጀት ዓመት የተጀመረው ይህ የእግረኛ መንገድ ግንባታ አምስት በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ተመራቂ ማህበራት በግንባታ ስራው ላይ እየተሳተፉበት የሚገኝ ሲሆን የግንባታ ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ አንድ አመት የግንባታ ጊዜም ተቆርጦለታል፡፡
ነባሩ የአያት ጣፎ የእግረኛ መንገድ በተለያየ ምክንያት ለብልሽት የተዳረገና በእግረኞች እንቅስቃሴ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታን ሲፈጥር የቆየ ነው፡፡
ይሄንን ችግር ለመፍታት በአካባቢው ዘመናዊ፣ ምቹና ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ እንዲኖር የሚያስችል የመልሶ ግንባታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ 3.3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገዱ ክፍል ታይልስ የለበሰ ሲሆን፣ በቀሪው የመንገዱ ክፍል ላይ ደግሞ የሰብ ቤዝ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ስራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን፣ በመንገዱ አካፋይ ላይ የአረንጓዴ ልማት እና የማስዋብ ስራዎች ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2016 በጀት ዓመት ከ48 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍን የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ ለማከናወን አቅዶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለፉት 6 ወራት ውስጥም 27.7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ አከናውኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity