+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የያዘው የሳይንስ ሙዚየም – ፍል ውሃ መንገድ መብራት

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የከተማዋን የምሽት የትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ከማድረግ ባለፈ፣ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ያካተቱ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው የመንገድ ዳር መብራቶችን ለአገልግሎት እያበቃ ይገኛል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራት አገልግሎት ተከላ ካከናወነባቸው አዳዲስ መንገዶች መካከል ከሳይንስ ሙዚየም – ፍል ውሃ የሚወስደው አቋራጭ መንገድ ይገኝበታል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ በተደረገው በእነዚህ መንገድ ላይ የተዘረጋው ዘመናዊ የመንገድ ዳር መብራት መስመር ከተለመደው አገልግሎት በተጨማሪ የትራፊክ ቁጥጥር ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ ነው።

በዚህ ስፍራ የተዘረጋው የመንገድ መብራት ካካተታቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ይዘቶች መካከል፤ የቀን እና የሌሊት ክዋኔዎችን አቅርበውና አጉልተው የሚቀርጹ CCTV ካሜራዎች፣ የአየር ሁኔታና የድምፅ ብክለት ጠቋሚ ሴንሰር፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ አገልግሎት የሚውል ቻርጂንግ እና ከትራፊክ ማስተዳደሪያ ማዕከል ጋር የተሳሰረ መቆጣጠሪያ የተገጠመለት መሆኑ ይጠቀሳሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ መረጃዎችን ማስተላለፍ የሚያስችል LED ስክሪን፣ ገመድ አልባ የበይነ-መረብ አገልግሎት እና የብልህ ብርሃን መስጫ ቴክኖሎጂዎችን አካቶ የያዘ መሆኑ የመንገድ መብራቱ የተለዩ ገፅታዎች ናቸው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በራስ ኃይል አቅም የገነባው ይህ መንገድ 450 ሜትር ርዝመት እና 40 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.