+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለፉት 6 ወራት ከ2,500 በላይ የውሃ መፋሰሻ መስመር ክዳኖች ጥገና ተከናውኗል

አዲስ አበባ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ባለፉት ስድስት ወራት በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች 2,542 በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተጎዱና ክፍት የሆኑ የውሃ መፋሰሻ መስመር ክዳኖችን (ማንሆል ክዳኖችን) መልሶ የመተካት ስራ አከናውኗል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአስፋልት መንገድ ጥገና ስራ ጎን ለጎን በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የማንሆል ክዳኖች በመለየት የጥገና ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በከተማዋ በብዛት የሚገኙት የኮንክሪት ማንሆል ክዳኖች በተሽከርካሪ ግጭት፣ በስርቆትና በተለያዩ ምክንያቶች ክፍት በመሆናቸው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚደርስውን ድንገተኛ አደጋ ለመከላከላልና የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የጥገና ስራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ 3,500 የሚሆኑ የተጎዱ ማንሆል ክዳኖችን ለመጠገን እና ለመቀየር በዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ 2,542 የማንሆል ክዳኖች መልሶ የመተካት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በቀጣይም ክፍት የሆኑ እና በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የማንሆል ክዳኖች የመጠገንና የመቀየር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የማንሆል ክዳን የጥገና ስራው የድሬኔጅ መስመሮች የዝናብ ውሃን በአግባቡ እንዲያስተናግዱ እና የመዲናዋ ጎዳናዎች ውብና ጽዱ ሆነው ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል በመሆኑ ሕብረተሰቡ የጋራ ሀብት የሆነውን መንገድ እና የመንገድ አካላትን በባለቤትነት ስሜት ከጉዳት እንዲጠብቅ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.