ባለፉት 6 ወራት ከ11 ሺ በላይ የመንገድ ዳር መብራቶች ተጠግነዋል
ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም – አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎት የማይሰጡና ጥገና የሚያስፈልጋቸውን 11 ሺ 296 የመንገድ ዳር መብራቶችን መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
የመንገድ ዳር መብራቶች በምሽት ወቅት የሚኖረውን የትራፊክ እንቅስቃሴ ሰላማዊና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከማስቻላቸው ባሻገር የከተማዋን ገፅታ ከመለወጥ አኳያም ያላቸው ሚና ጉልህ ነው፡፡ ህብረተሰቡም ላይ ጨለማን ተገን ተደርጎ የሚደርሰውን ስርቆትና ዝርፊያን ለመቀነስ እነዚህ የመንገድ ዳር መብራቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡
ከዚህ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት በቁጥር 4810 የሚሆን የመንገድ ዳር የመብራት ምሶሶዎችን ለመጠገን ታቅዶ 7,097 ያህሉን ለማከናወን ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ 1,110 የሚሆኑ የማይሰሩና ለእይታ የሚያስቸግሩ አምፖሎች ለመቀየር ታቅዶ 4199 አምፖሎችን የመቀየር ስራ ተከናውኗል፡፡
በመሆኑም ባለስልጣኑ በከተማችን በስርቆትና በተለያየ ምክንያት ለብልሽት ተዳርገው አገልግሎት መስጠት ያቆሙና በህብረተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያስነሱ የነበሩ የመንገድ ዳር መብራቶችን በመጠገን አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት ሥራው ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ከመለስ ፋውንዴሽን በሴቶች አደባባይ – አቧሬ፣ ከቡናና ሻይ – ልደታ ፍርድ ቤት፣ ከፍል ውሃ- ኢትዮጲያ ሆቴል፣ ከጎተራ – ወሎ ሰፈር፣ ከደንበል – ወሎ ሰፈር፣ ልደታ ፀበል – ቡልጋሪያ፣ ከዊንጌት – አስኮ፣ ኮልፌ አደባባይ – ጦር ሃይሎች፣ ከፓስተር – ዊንጌት ፣4 ኪሎ አካባቢ፣ ከብስራተ ገብርኤል ጤና ጣቢያ – መከኒሳ አቦ፣ ቦሌ ማተሚያ አካባቢ፣ ሜክሲኮ አደባባይ – ብሄራዊ፣ ከአዲስ ሰፈር -ሎሚ ሜዳ፣ ከጦር ሃይሎች – ቀራኒዬ፣ አሚጎ ካፌ- ቆሬ፣ ከአቡነ ጴጥሮስ – ዩሃንስ ቤተክርስቲያን፣ ቤተመንግስት አካባቢ፣ ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ፣ የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም እና ከ4 ኪሎ – ቀበና ያሉ ጎዳናዎች ይገኙበታል፡፡
በአጠቃላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2016 በጀት ዓመት በቁጥር 16 ሺህ የመንገድ መብራቶችን ለመጠገንና ደረጃቸውን ለማሻሻል አቅዶ እየሰራ ሲሆን ባለፉት 6 ወራት ከ11 ሺህ በላይ የመንገድ መብራት ጥገናና ማሻሻያ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity